Time in Ethiopia:

Thursday, April 3, 2014

ሐተታ ዘርዓ ያዕቆብ

Ethiopian Argument | Thursday, April 03, 2014
እግዚያብሔርን የምትፈሩ ሁሉ ለነፍስ ያደረጋችሁትን መናገር እጀምራለሁና ኑ ስሙኝ፡፡ ሁሉን በፈጠረ መጀመሪያና መጨረሻ በሆነ ሁሉን በያዘና የህይወትና የጥበብ ሁሉ ምንጭ በሆነ እግዚያብሔር በሰጠኝ ረዥም እድሜየ ትንሽ እፅፋለው፡፡ ነፍሴ በእግዚያብሔር ዘንድ የተከበረች ትሁን ጆሮዎችም ሰምተው ይደሰቱ፡፡ እኔ እግዚያብሔርን ፈለኩት መለሰልኝ፡፡ አሁንም እናንተ ወደ እርሱ ቅረቡ ያበራላችሁማል ፊታችሁንም አያሳፍርም፡፡ እግዚያብሔርን ከኔ ጋር ከፍ ከፍ አድርጉት አብረን ስሙን እናንሳ፡፡ 
እኔ የተወለድኩት በአክሱም በካህናት ሀገር ነው፡፡ ነግር ግን እኔ በአክሱም አውራጃ አፄ ዘርዓ ያዕቆብ በነገሰ በሶስተኛው ዓመት በ1592 ዓ/ም ከ አንድ ገበሬ ቤተሰብ ተወለድሁ፡፡ በክርስትና ጥምቀት ዘርዓ ያዕቆብ ተብየ ተሰየምኩ፡፡ ሰወች ግን ወርቄ ይሉኛል፡፡ ካደኩ በኋላ ትምህርት እንድማር አባቴ ወደ ትምህርት ቤት ላከኝ፡፡ ዳዊትም ከደገምኩ በኋላ መምህሬ አባቴን ይህ ህፃን ልጅህ ልቦናው የበራ በትምህርት ታጋሽ ነውና ወደ ትምህርት ቤት ብትልከው ሊቅና መምህር ይሆናል አለው፡፡ አባቴም ይህን ሰምቶ ዜማ እንድማር ላከኝ፡፡ ሆኖም ድምጼ ሸካራ ሆኖ አላምር አለኝ፡፡ በዚህ ምክንያት ደኞቼ መሳቂያና መዘባበቻ
አደረጉኝ፡፡ እዛም ሶስት ወር ያህል ቆየው፡፡ ስላልተሳካልኝ ከልቤ አዘንኩ፡፡ ተነስቼ ሰዋሰውና ቅኔ ለመማር ወደ ሌላ አስተማሪ ሄድኩ፡፡ ከደኞቼ ፈጥኜ እንድማርም እግዚያብሔር ጥበቡን ሰጠኝ፡፡ ይህም የመጀመሪያ ሃዘኔን አስረሳኝ ፡፡ በጣም ተደሰትኩ፡፡ እዛም አራት አመት ቆየሁ፡፡ በነዚያ ቀኖች እግዚያብሔር ከሞት አዳነኝ፡፡ ከደኞቼ ጋር ስጫወት ወደገደል ወደኩ፡፡ እግዚያብሔር በታምራቱ አዳነኝ እነጅ ፈፅሞ ልድን አልችልም ነበር፡፡ ከዳንኩ በኋላ ገደሉን በረዥም ገመድ ለካሁት፡፡ አስራ ሶስት ሜትር ሆኖ ተገኝ፡፡ እኔም ድኜ ያዳነኝን እግዚያብሔርን እያመሰገንኩ ወደ መምህሬ ቤት ሄድኩ፡፡ ከዚያም ተነስቼ የቅዱሳት መፅሃፍትን ትርጉዋሜ ለመማር ሄድኩ፡፡ በዚያም አስር ዓመት ቆየሁ፡፡ መፅሃፍትን ፈረንጆች እንዴት እነደሚተረጉሟቸው የኛም ምሁራን እንዴት እነደሚተረጉሟቸው ተማረኩ፡፡ ትርጉዋሜያቸው ግን ከኔ ልቦና ጋር የሚስማማ አልነበረም፡፡ ሆኖም ይህን ስሜቴን ሃሳቤን ለማንም ሳልገልፅ በልቤ  ይዥው ቆየሁ፡፡ ከዚያም ወደሃገሬ ወደ አክሱም ተመለስኩ፡፡ በአክሱም ለ አራት አመት መፅሃፍ አስተማረኩ፡፡ ይህ ዘመን ክፉ ዘመን ሆነ፡፡ አፄ ሱስንዮስ በነገሰ በ 19ኛው ዓመት የፈረንጆች ተወላጅ አቡነ አልፎንዝ መጣ፡፡ ከ 2 ዓመት በኋላም ንጉሱ የፈረንጆቹን  ሃይማኖት ስለተቀበለ በኢትዮጵያ ትልቅ ስደት ሆነ፡፡ ይህን  ሃይማኖት ያልተቀበለ በሙሉ ግን እጣው ስደት ሆነ፡፡

አፄ ሱስንዮስ፣ አልፎንዝና ጠላቴ ወልደ ዩሃንስ
እኔ በሃገሬ መፅሃፍት ሳስተምር ብዙዎቹ ጓደኞቸ ጠሉኝ፡፡ በዚህ ዘመን የባልንጀራ ፍቅር ጠፍቶ ነበርና ቅናት ያዛቸው፡፡ በትምህርትና ጓደኛን በመውደድ ከነርሱ እበልጣለው፡፡ ከሁሉ ሰው፤ ከፈረንጆቹና ከግብፃዊያን ጋር እስማማለሁ፡፡ መፅሃፍትን ሳስተምርና ስተረጉም እንዲህ እንዲህ ይላሉ፡፡ ግብፃዊያኖች ደግሞ (ኦርቶዶክሶች) እንዲህ እንዲህ ይላሉ እላለው፡፡ እኛም ብንመረምር ይህን ሁሉ እናውቃለን እላለሁ እንጅ ይህ መልካም ነው ይህ ደግሞ ክፉ ነው አልልም፡፡ ግብፃቹ የፈረንጅ፣ ፈረንጆቹ ደግሞ የግብፃዊያኖቹ እመስላቸዋለው፡፡ ስለዚህ ሁሉም ጠሉኘ፡፡ ብዙ ጊዜም ወደንጉሱ ከሰሱኝ፡፡ እግዚያብሔር ግን አዳነኝ፡፡ ከዚህም በኋላ ከአክሱም ካህናት አንድ ወልደ ዮሃንስ የተባለ ጠላቱ የንጉስ ወዳጅ ስለነበረ፣ የነገስታት ፍቅር በሽንገላ ምላስ ስለሚያገኝ ወደ ንጉሱ ሄደ፡፡ ወደ ንጉሱም ገብቶ እንደዚህ አለው ፡፡
“ይህ ሰው ህዝብን ያሳስታል፡፡ ስለሃይማኖታችን እንነሳና ንጉሱን እንግደለው፣ ፈረንጆቹንም እናባራቸው ይላል”
 እያለ ይሄንና ይሄን በመሰለ ውሸት ከሰሰኝ፡፡ እኔም ይህን አውቄ ገና ለገና ይገድለኛል ብዮ ፈርቼ የነበረኝን ሶስት ወቄት ወርቅና የምፀልይበትን መዝሙረ ዳዊት ይዠ በሌሊት ሸሸሁ፡፡ ወዴት እነደምሄድ ለማንም አልተናገርኩም፡፡ ወደተከዜ በረሀ ገባሁ፡፡ በነጋታውም ራበኝ፡፡ ከሀብታሞች ገበሬዎች እንጀራ ለመለምን እየፈራሁ ወጣሁ፡፡ ሰጡኝና በልቼ እየሮጥኩ ሄድኩ፡፡ እንዲህ እያልኩ ብዙ ቀን ቆየሁ፣ በኋላ ወደ ሽዋ ግድም ስሄድ ሰው የለለበት በርሃ አገኝሁ፡፡ ከገደሉ በታች መልካም ዋሻ ነበርና ሰው ሳያየኝ በዚህ ዋሻ  እኖራለሁ ብየ ወሰንኩ፡፡ ሱስንዮስ እስኪሞትም ድረስ በዚያ 2 ዓመት ቆየሁ፡፡ አንዳድንዴ ወደገበያ እየወጣው ወይም ወደ አማሮች ሀገር እሄድ ነበር፡፡ ለአማራ ሰዎች የምበላው እንዲሰጡኝ  የምለምን ባህታዊ መነኩሴ እመስላቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ሰዎች ከየት እንደምወጣና ወዴት እነደምገባ አያውቁም፡፡ ከዋሻየ ለብቻየ በሆንኩ ጊዜም በመንግስተ ሰማያት የምኖር መሰለኝ፡፡ ቁጥር የሌለው ክፋታቸውን አውቄ ከሰዎች ጋር መኖር ጠላሁ፡፡ ሌሊት መጥተው የበርሃ አራዊት እንዳይበሉኝም በድንጋይና በአሽዋ አጥር ዋሻየን አጠረኩ፡፡ እሚፈልጉኝ ሰዎች ወደኔ ቢመጡ የማመልጥበት መውጫ አዘጋጀሁ፡፡ እዛ በሰላም ኖርኩ፡፡ በሚሰማኝ በእግዚያብሔር ተስፋ አድርጌ በሙሉ ልቤ በመዝሙረ ዳዊት ፀለይኩ፡፡
ስለአምላክ መኖርና የሐይማኖት መለያየት
ከፀሎት በኋላም ስራ ስለሌለኝ ሁልጊዜ ስለሰዎች ክፋትና ሰዎች በእርሱ ስም ሲበድሉ፣ ወንድሞቻቸውን ጉዋደኖቻቸውን ሲያባርሩ እና ሲገድሉ ዝም በማለቱ ስለፈጣሪ ጥበብ አስብ ነበር፡፡ በዚህም ጊዜ ፈረንጆቹ አየሉ፡፡ ነገር ግን ያገሩ ሰዎችም ከነሱ የባሰ ክፋት ሰሩ እንጅ ፈረንጆቹ ብቻቸውን አልነበረም የከፉት፡፡ የካቶሊክ ሃይማኖት የተቀበሉት ኦርቶዶክሶች የመንበረ ጴጥሮስን እውነተኛዋን ሃይማኖት ክደዋልና የእግዚያብሔር ጠላቶች ናቸው አሉ፡፡ ስለዚህም አሳደዱአቸው፡፡ ኦርቶዶክሶችም ለሃይማኖታቸው እንዲሁ አደረጉ፡፡
እግዚያብሔር የሰዎች ጠባቂ ከሆነ ለምን ፍጥረታቸው እንዲህ ከፋ ብየ አሰብኩ፡፡ በአርያም የሚያውቅ አለን ? ኧረ እግዚያብሔርስ ያውቃልን ? በቅዱስ ስሙ ሲበድሉና ሲረክሱ የሚያውቅ ከሆነ እንዴት የሰዎችን ክፋት ዝም ይላል? አልኩ፡፡ ምንም ልብ አላደረኩም ብዙ አሰብኩ፡፡ የፈጠርከኝ  ፈጣሪየ ሆይ አዋቂ አድርገኝ፤ የተደበቀውን ጥበብህን ንገረኝ ብየ ፀለይኩ፡፡ ለሙት እንዳይተኙ አይኖችህን አብራቸው እጆችህ አደረጉኝና ሰሩኝ፡፡ ትዕዛዝህን እንድማር ልብ ስጠኝ፡፡ ለኔ ግን እግሮቼ በተፍገመገሙ፤ ተረከዞቸም በተንሸራተቱ ነበር ፡፡ ይህም በፊቴ ስላለው ድካም ነው፡፡ ይህንን እና ይህን የመሰለ ፀሎት አደርግ ነበር፡፡
አንድ ቀን እኔ ወደ ማን ነው የምፀልየው አልኩ፡፡ በእውነት የሚሰማኝ እግዚያብሔር አለን? በዚህም አሳብ በጣም አዝኜ እንዲህ አልኩ ፡፡ ዳዊት እንዳለ እንዴት  ምንኛ ልቤን አፀደኳት፡፡ ኋላም አሰብኩ ይህ ዳዊት እንዲህ የሚለው ጆሮን የተከለ አይሰማምን ? በእውነት እንድሰማበት ጆሮ የሰጠኝ ማነው? አዋቂስ አድርጎ የፈጠረኝ ማነው? በዚህስ አለም እኔ እንደምን መጣሁ? ከዓለም በፊት ብኖር የህይወቴ መጀመሪያና የእውቀቴ መጀመሪያን ባወኩ፡፡ እኔ በገዛ እጄ ተፈጠርኩን ? ነገር ግን እኔ በተፈጠርኩ ጊዜ አልኖርኩም፡፡ አባት እናቴ ፈጠሩኝ ብልም እንደገና ወላጆችና የወላጆችን ወላጅ፣ወላጅ የሌላቸው በሌላ መንገድ ወደዚህ ዓለም የመጡትን እንደኛ ያልተወለዱትን የፊተኞቹ ድረስ ፈጣሪያቸውን እፈልጋለሁ፡፡ እነርሱም ቢወለዱ የፈጠራቸው አንድ ህላዌ አለ ከማለት በቀር የጥንት መወለጃቸውን አላውቅም፡፡ ያለና በሁሉም የሚኖር የሁሉ ጌታ ሁሉን የያዘ መጀመሪያና መጨረሻ የሌለው ዓመቱ እማይቆጠር እማይለወጥ ያልተፈጠረ ፈጣሪ አለ አልኩ፡፡ ፈጣሪስ አለ፡፡ ፈጣሪ ባይኖር ፍጥረት ባልተገኘ አልኩ፡፡ እኛ ብንኖር ፍጡራን እንጅ ፈጣሪዎች አይደለንም፡፡ የፈጠረ ፈጣሪ አለ እንል ዘንድ ይገባናል፡፡ ይህም የፈጠረን ፈጣሪ አዋቂና ተናጋሪ ካልሆነ በቀር ከዕውቀቱ በተረፈ አዋቆዎችና ተናጋሪዎች አድርጎ ፈጥሮናል፡፡ ሁሉን ፈጥሯል ሁሉን ይይዛልና እርሱ ሁሉን ያውቃል፡፡ ፈጣሪየ ወደ እርሱ ስፀልይ ይሰማኛል ብየ ሳስብ ትልቅ ደስታ ተደሰትኩ፡፡ በትልቅ ተስፋም እየፀለይኩ ፈጣሪየን በሙሉ ልቤ ወደድኩት፡፡ ጌታየ ሆይ አንተ ሃሳቤን ሁሉ ከሩቅ ታውቃለህ አልኩት፡፡ አንተ የመጀመሪያየ ነህ፡፡ የመጨረሻየን ሁሉን አወቅህ፡፡ መንገዴንም ሁሉ አንተ አስቀድመህ አወቅህ፡፡ ስለዚህም ከሩቅ ታውቃለህ ይሉሃል፡፡ እኔ ሳልፈጠር ሀሳቤን ያውቃልና ፈጣሪየ ሆይ እውቀትን ስጠኝ አልኩ፡፡
ስለ ሃይማኖት ምርመራና ፀሎት
በኋላም ይህ በቅዱስ መፅሃፍት የተፃፈ ሁሉ እውነት ይሆን? ብየ አሰብኩ፡፡ በጣም አላወኩምና የተማሩና ተመራማሪ ሰዎች እውነቱን እንዲነግሩኝ ሄጄ ልጠይቃቸው ብዮ ብዙ አሰብኩ፣ እንደገናም ሰዎች በየልባቸው ያለውን ካልሆነ በቀር ሌላ ምን ይመልሱልኛል ብየ አሰብኩ፡፡ ሰው ሁሉ የኔ ሃይማኖት እውነተኛ ናት ይላል፡፡ በሌላ ሃይማኖት የሚያምኑ ሐሰተኞች የእግዚያብሔር ጠላቶች ናቸው፡፡ ዛሬም ቢሆን ፈረንጆች ሃይማኖታችን መልካም ናት፣ ሃይማኖታችሁ ግን መጥፎ ናት ይሉናል፡፡ እኛም መልሰን እንዲዚህ አይደለም የናንተ ሃይማኖት መጥፎ የኛ ሃይማኖት ግን መልካም ናት እንላቸዋለን፡፡ እንደገናም የእስልምና፣ የአይሁድ አማኞችን ብንጠይቃቸው እንዲሁ ይሉናል፡፡ በዚህም ክርክር ፈራጅ ማን ይሆናል፡፡ ሰዎች ሁሉ እርስ በእርሳቸው ወቃሾችና ተወቃሾች ሆነዋል፡፡ አንድ እንኳን ከሰው ልጅ የሚፈርድ አይገኝም፡፡ እኔ መጀመሪያ ስለብዙ ሃይማኖቶች ጉዳይ አንድ የፈረንጅ መምህር ጠየኩ፡፡ እሱ ግን ሁሉን እንደራሱ ሀይማኖት አድርጎ ፈታው፡፡ ኋላም አንድ ትልቅ የኢትዮጵያ መምህር ጠየኩ ፡፡ እርሱም ሁሉን እነደ ሃይማኖቱ አድርጎ ተረጎመው፡፡ እስልምና እና አይሁድንም ብንጠይቅ እንዲሁ እንደ ሃይማኖታቸው ይተረጉማሉ፡፡ ታዲያ እውነት የሚፈርድ የት አገኛለሁ? የኔ ሃይማኖት ለኔ ትክክል እንደሚመስለኝ እንዲሁ ለሌላውም ሃይማኖቱ እውነት ይመስለዋል፡፡ ነገር ግን ፅድቅ አንዲት ብቻ ናት፡፡
እንደዚህ እያልኩ አሰብኩ፡፡ ጠቢብና የእውነተኞችም እውነተኛ እኔን የፈጠርክ ሆይ አዋቂ አድርገህ የፈጠርከኝ ሆይ ዳዊት ሰው ሁሉ ዋሾ ነው ካለው በስተቀር በሰው ዘንድ ጥበብና እውነት አይገኝምና አንተ አዋቂ አድርገኝ ብዮ ፀለይኩ፡፡ ሰዎች በዚህ ትልቅ ነገር ነፍሳቸውን ለማጥፋት ስለምን ይዋሻሉ? ብየ አሰብኩ፡፡ የሚዋሹም መሰለኝ፡፡ የሚያወቁ እየመሰላቸው ምንም አያውቁምና የሚያውቁ ይመስላቸዋል፡፡ ስለዚህ እውነትን ለማግኝት ብለው አይመረምሩም፡፡ ዳዊት እንዳለው ልባችን እንደወተት ረካ፡፡ ከአባቶቻቸው በሰሙት ልባቸው ረክቷል፡፡ እውነት ወይም ሀሰት ሊሆን ይችላል ብለው አልመረመሩም፡፡ እኔም ጌታ ሆይ ፈርድህን  እንዳውቅ ያሳመንከኝ ይገባኛል አልኩ፡፡ አንተ በእውነት ቅጣኝ፣ በምህረትህም ገስፀኝ፡፡ አንተ አዋቂ አድርገህ የፈጠርከኝ ጥበበኛ አድርገኝ እንጅ የዋሾ መምህራንና የሐጢያት ቅባት እራሴን አልቀባም፡፡ እኔ አዋቂ ብሆን ምን አውቃለው ብየ አሰብኩ፡፡ ከፍጥረት ሁሉ የሚልቅ ፈጣሪ እንዳለ አውቃለሁ፡፡ ከታላቅነቱ የተረፈ ታላላቅን ፈጥሯልና፡፡ ሁሉንም የሚያውቅ ነውና፡፡ ከአዋቂነቱ በተረፈ አዋቂዎች አድርጎ ፈጥሮናልና፡፡ ለርሱ ልንሰግድለት ይገባል፡፡ እርሱ የሁሉ ጌታና ሁሉንም የያዘ ነውና ወደርሱ በፀለይን ጊዜ ይሰማናል፡፡ እግዚያብሄር አዋቂ አድርጎ የፈጠረኝ በከንቱ አይደለም፡፡ እንዲህ አድርጎ የፈጠረኝ እንድፈልገውና እርሱ በጥበቡ በፈጠረኝ መንገድ እንዳውቀው እስካለሁም ድረስ እንዳመሰግነው ነው  ብየ አሰብኩ፡፡ ሰዎች ሁሉ ሀሰት ካልሆነ በስተቀር ስለምን እውነት አይናገሩም ብየ አሰብኩ፡፡ የሰው ፍጥረት ታካችና ደካማ መሰለኝ፡፡ ሰው ግን ፍቅርን ቢወዳትና በጣም ቢያፈቅራት የተሸሸገውንም ፍጥረትን ቢያውቅ ይወዳል፡፡ ይህም ነገር እጅግ ጥልቅ ነውና በትልቅ ድካምና ትዕግስት ካልሆነ በስተቀር አይገኝም፡፡
ጠቢቡ ሰለሞን፡
“ከፀሐይ በታች ስለተደረገው ሁሉ ጥበብን ለመፈለግና ለመመርመር ልቤን ሰጠሁ፡፡ እግዚያብሔር ለሰው ልጆች እንዲደክሙበት የሰጣቸውን ክፉ ስራ አየሁ” ይላል፡፡
ስለዚህ ሰዎች ሊመረምሩት አይፈልጉም፡፡ ሳይመረምሩ ከአባቶቻቸው የሰሙትን ማመን ይመርጣሉ፡፡ ነገር ግን እግዚያብሔር ሰውን የምግባሩ ጌታ ክፉ ወይም መልካም የፈለገውን እንዲሆን ፈጠረው፡፡ ሰውም ክፉና ዋሾ መሆንን ቢመርጥ ለክፋቱ የሚገባውን ቅጣት እስኪያገኝ ድረስ ይችላል፡፡
ነገር ግን ሰው ስጋዊ ነውና ለስጋው የሚመቸውን  ይወዳል፡፡ ክፉ ይሁን መልካም ለስጋው ፍላጎት የሚያገኝበትን መንገድ ሁሉ ይፈልጋል፡፡ እግዚያብሔር ሰው የፈለገውን እንዲሆን ለመምረጥ መብት ሰጠው እንጂ ለክፋት አልፈጠረውም፡፡ ስለዚህ መምረጥ ክፉ ቢሆን ለቅጣት መልካም ቢሆን ደግሞ የመልካምነት ዋጋ ለመቀበል የተዘጋጀ እንዲሆን እድል ሰጠው፡፡ በህዝብ ዘንድ ክብርና ገንዘብ ለማግኝት የሚፈልግ ዋሾ ሰው ነው፡፡ ዋሾ ሰው ይህን በሐሰተኛ መንገድ ሲያገኝ እዉነት አስመስሎ ሀሰት ይናገራል፡፡ ሊመረምሩ የማይፈልጉ ሰዎች እውነት ይመስላቸውና በእርሱ በፅኑ ሃይማኖት ያምናሉ፡፡ እስኪ ህዛባችን በስንት ውሸት ያምናል? በጽኑ ሃይማኖት ያምናል፡፡ በሃሳበ ከዋክብትና በሌላም አስማት፣ አጋነንት በመሳብና በመርጨት፣ አስማት በማድረግ፣ በጥንቆላ ሁሉ ያምናሉ፡፡ ይህንን ሁሉ መርምረው እውነቱን አግኝተው አያምኑም፡፡ ነገር ግን ከአባቶቻቸው ሰምተው ያምናሉ፡፡ እነዚያስ የፊተኞቹ ገንዘብና ክብር ለማግኝት ካልሆነ በቀር ስለምን ዋሹ? እንዲሁ ህዝብን ሊገዙ የሚፈልጉ ሁሉ እውነት እንነግራቸኋለን እግዚያብሔር ወደናንተ ላከን ይሏቸዋል፡፡ ህዝቡም ያምናሉ፡፡ ከነርሱም በኋላ የመጡት እነርሱ ሳይመረምሩ የተቀበሏትን ያባቶቻቸውን እምነት አልመረመሩም፡፡ ከዛ ይልቅ ለእውነት ለሃይማኖታቸው ማስረጃ ታሪክን፣ ምልክቶችን ፣ ተዓምራትን እየጨመሩ አፀኑት፡፡ እግዚያብሔርንም የሐሰኞች ተካፋይና የሐሰት ምስክር አደረጉት፡፡
ጥልቅ ምርመራ ስለ ሙሴና መሐመድ ሕግጋት
ለሚመረምር ግን እውነት ቶሎ ይገለፃል፡፡ ፈጣሪ በሰው ልብ ያስገባውን ንፁህ ልቦና የፍጥረት ሕግጋትና ስርዓትን ተመልክቶ የሚመረምር እርሱ እውነትን ያገኝል፡፡ ሙሴ ፈቃዱንና ሕጉን ልነግራችሁ ከእግዚያብሔር ዘንድ ተልኬ መጣሁ ይላል፡፡ ከርሱ በኋላ የመጡት በግብፅና በደብረሲና እንዲህ ተደረገ እያሉ ታሪክን፣ ተዓምራትን እየጨመሩ የሙሴን ነገር እውነት አስመሰሉት፡፡
የሙሴ መፅሃፍ ከፍጥረት ሕግ ሰርዓትና ከፈጣሪ ጥበብ ጋር አይስማማም፡፡ ከውስጡ የተሳሳተ ጥበብ ይገኛል፡፡ ለሚመረምር ግን እውነት አይመስለውም፡፡ በፈጣሪ ፈቃድና በፍጥረት ህግ የሰው ልጅ እንዳይጠፋ ልጆችን ለመውለድ ወንድና ሴት በፍትወተ ስጋ እንዲገናኙ ታዟል፡፡ ይህም ግንኙነት እግዚያብሔር ለሰው በሕገ ተፈጥሮ የሰጠው ነው፡፡ እግዚያብሔርም የእጁን ስራ አያረክስም፡፡ እግዚያብሔር ዘንድ እርኩሰት ሊገኝ አይችልም፡፡ ሙሴ ይህን ማለቱ ትክክል ነው አልልም፡፡ ፈጣሪውን ዋሾ  እንዳደረገው ልቦናችን ያስረዳናል፡፡ እንደገናም የክርስቲያን ሕግ ለማስረጃዋ ተአምራቶች ተገኝተዋልና ከእግዚያብሔር ናት ይላሉ፡፡ ነገር ግን የወሲብ ስርዓት የተፈጥሮ ስርዓት እንደሆነ ምንኩስና ግን ልጆች ከመውለድ ከልክሎ የሰውን ፍጥረት አጥፍቶ የፈጣሪን ጥበብ የሚያጠፋ እነደሆነ ልቦናችን ይነግረናልና ያስረዳናል፡፡ የክርስቲያን ሕግ ምንኩስና ከወሲብ ይበልጣል ብትል ሐሰት ትናገራለችና ከእግዚያብሔር አይደለችም፡፡ የፈጣሪን ሕግ የሚያፈርስ እንዴት ከጥበብ በለጠ ? ወይስ የእግዚያብሔርን ስራ የሰው ምስክር ሊያስተካክለው ይቻለዋልን ?
እንዲሁም መሐመድ የማዛችሁ ከእግዚያብሔር የተቀበልኩትን ነው ይላል፡፡ መሐመድን መቀበል የሚያስረዱ ተዓምራት ፀሐፊዎች አልጠፉምና ከሱም አመኑ፡፡ እኛ ግን የመሐመድ ትምህርት ከእግዚያብሔር ሊሆን እንደማይችል እናውቃለን፡፡ የሚወለዱ ሰዎች ወንድና ሴት ቁጥራቸው ትክክል ነው፡፡ በአንድ ሰፊ ቦታ የሚኖሩ ወንድ ሴት ብንቆጥር ለእያንዳንዱ ወንድ አንዲት ሴት ትገኛለች እንጂ ለአንድ ወንድ ስምንት ወይም አስር ሴቶች አይገኙም፡፡ የተፈጥሮ ህግም አንዱ ከአንዲት ጋር እንዲጋቡ አዟል፡፡ አንድ ወንድ አስር ሴት ቢያገባ ግን ዘጠኝ ወንዶች ሴት የሌላቸው ይቀራሉ፡፡ ይህም የፈጣሪን ስርዓትና ሕገ ተፈጥሮን የጋብቻንም ጥቅም ያጠፋል፡፡ አንድ ወንድ ብዙ ሴቶች ሊያገባ ይገባዋል ብሎ በእግዚያብሔር ስም ያስተማረ መሐመድ ግን ትክክል ነው አልልም፡፡ ከእግዚያብሔር ዘንድ አልተላከም፡፡
ጥቂት ስለጋብቻ ሕግ መረመርኩ ፡፡ የቀረውን ብመረምርም በህገ ኦሪትና በክርስትና በእስልምና ሕግ ፈጣሪ በልቦናችን ከሚገልፅልን እውነት እና እምነት አይስማማም፡፡ ብዙ አይገኝበትም አልኩ፡፡ ፈጣሪ ለሰው ልጅ ክፉና መልካም የሚለይበት ልቦና ሰጥቶታል፡፡ በብርሀን ብርሀን እናያለን እንደተባለውም የሚገባውን የማይገባውን ሊያውቅ፣ እውነትን ከሐሰት እንዲለይ ነው፡፡ ስለዚህ የልቦናችን ብርሀን እንደሚገባ በእርሱ ብናይበት ሊታይልን አይችልም፡፡ ፈጣሪያችን ይሄን ብርሃን የሰጠን በርሱ እንድንድን ነው እንጅ እንድንጠፋ አይደለም፡፡የልቦናችን ብርሀን የሚያሳየን ሁሉም ከእውነት ምንጭ ነው፡፡ ሰዎች ከሐሰት ምንጭ ነው ቢሉን ግን ሁሉን የሰራ ፈጣሪ ቅን እንደሆነ ልቦናችን ያስረዳናል፡፡ ፈጣሪ በመልካም ጥበቡ ከሴት ልጅ ማህፀን በየወሩ ደም እንዲፈስ አዟል፡፡ ሙሴና ክርስቲኖች ግን ይህን የፈጣሪ ጥበብ እርኩስ አደረጉት፡፡
እንደገና ሙሴ እንዲህ ያለችውን ሴት የተገናኛት ያረክሳል፡፡ ይህም የሙሴ ህግ የሴትን ኑሮ በሙሉና ጋብቻዋን ከባድ አድርጎታል፡፡ የመራባትንም ህግ አጥፍቷል፡፡ ልጆችንም ከማሳደግ ከልክሎ ፍቅርንም ያፈርሳል፡፡ ስለዚህ ይህ የሙሴ ሕግ ሴትን ከፈጠረ ሊሆን አይችልም፡፡ እንደገናም የሞቱትን ወንድሞቻችንን ልንቀብራቸው ተገቢ መሆኑን ልቦናችን ይነግረናል፡፡ በድኖቻቸውም በሙሴ ጥበብ ካልሆነ በስተቀር ከመሬት የተፈጠርንበት ወደመሬትም ልንገባባዘዘን በፈጣሪያችን ጥበብ እርኩሳን አይደሉም፡፡ ነገር ግን ለፍጥረት ሁሉ እንደሚገባ በትልቅ ጥበብ የሰራ እግዚያብሔር ስርዓቱን አያረክሳውም፡፡ ሰው ግን የሐሰትን ቃል እንዲያከብር ብሎ ሊያረክሰው ይፈልጋል፡፡
እንደገና ወንጌል አባት እና እናቱን ምሽቱን እና ልጁን ያልተወ ለእግዚያብሔር የተገባ አይሆንም ይላል፡፡ ይህ መተው የሰውን ፍጥረት ሁሉ ያጠፋል፡፡ እግዚያብሔር ግን ፍጥረቱን በማጥፋት አይደሰትም፡፡ አባትና እናትም በሽምግልናቸው ጊዜ እረዳት አተው እንዲሞቱ መተው ትልቅ አበሳ መሆኑን ልቦናችን ያሳየናል፡፡ እግዚያብሔርም አመፃን የሚወድ አምላክ አይደለም፡፡ ልጆችን መተው ግን ከበረሃ አራዊት ይብሳሉ፡፡ ምሽቱ ስታመነዝር የሚፈታት ሁሉ የፈጣሪን ስርዓትና የተፈጥሮን ሕግ አፍርሷል፡፡ ስለዚህም ወንጌል በዚህ ስፍራ የሚለው ከእግዚያብሔር ሊሆን አይችልም፡፡
እንደገና በእስልምና ሰው እንደ እንስሳ ሊሸጥና ሊገዛ ይገባል ይላሉ፡፡ ፈጣሪያችን እንደ ወንድሞች አስተካክሎ ከፈጠረን ከሰዎች ፈጣሪ ይህ የእስልምና ህግ ሊወጣ አይችልም፡፡ ልቦናችን ያውቃል እነሱ ግን ደካማን ሰው የሐይለኛ ሰው ንብረት አደረጉት፡፡ አዋቂው ፍጥረትንም ካላዋቂው እንስሳ ጋር አስተካክሎት ይህ ከእግዚያብሔር ዘንድ ሊወጣ ይችላልን ?
እንደዚሁም እግዚያብሔር የከንቱ ነገር አያዝም፡፡ ይህን ብላ፣ ይህን አትብላ፣ ዛሬ ብላ፣ ነገ አትብላ አይልም፡፡ ለክርስቲያኖች እንደሚመስላቸውና የጾም ሕግጋት እንደሚጠብቁ ስጋን ዛሬ ብላ ነገ አትብላ አይልም፡፡ ለክርስቲያኖች እንደሚመስላቸውና የጾም ሕግጋት እንደሚጠብቁ ስጋን ዛሬ ብላ ነገ ግን አትብላ አይልም፡፡ እስላሞችንም  እግዚያብሔር ለሊት ብሉ ቀን አትብሉ ብሎ ይሄንና የመሳሰሉትን አይላቸውም፡፡ የፍጥረታችንን ጤና የማያውክ ነገር ሁሉ ልንበላ እንደሰለጠንን ልቦናችን ያስተምረናል አንድ የመብል ቀን አንድ የጾም ቀን ግን ጤናን ያውካል፡፡ የጾም ህግ መብላትን ለሰው ሕይወት ከፈጠረና ልንበላቸው ከፈቀደ ፈጣሪ የወጣ አይደለም፡፡ በልተን ልናመሰግነው እንጅ በረከቱን ልናርም አይገባንም፡፡ ሕገ ፆም የስጋን ፍትወት ለመግደል የተሰራ ነው የሚሉም ቢኖሩ ፍትወተ ስጋ ወንድ ወደ ሴት ሊሳብ ሴትም ወደ ወንድ ልትሳብ የፈጣሪ ጥበብ ነውና እርሱ ፈጣሪ በሰራው በታወቀ ማጥፋት አይገባም እላለሁ፡፡
ፈጣሪያችን ይህን ፍትወት ለሰው ለእንስሳት ሁሉ በከንቱ አልሰጠም፡፡ ነገር ግን ለዚህ ዓለም ሕይወትና ለፍጥረት የተሰራለት መንገድ ሁሉ መሠረቱ ሆኖ እንዲቆይ ይህ ፍትወት ለሰው ልጅ ተሰጠ፡፡ አስፈላጊያችን ልንበላ ይገባናል፡፡ በእሁድ ቀንና በበዓል ቀናት በአስፈላጊው ልክ የበላ እንዳልበደለ እንዲሁ በአርብ ቀንና ከፋሲካ በፊት ባሉት ቀናት ለክቶ የሚበላ አልበደለም፡፡ እግዚያብሔር ሰውን በሁሉ ቀንና በሁሉ ወራት ካስፈላጊ ምግብ ጋር አስተካክሎ ፈጥሮታል፡፡ አይሁድ፣ ክርስቲያንና እስላም ግን የፆምን ሕግ ባወጡ ጊዜ ይህን የእግዚያብሔር ሥራ ልብ አላሉም፡፡ እግዚያብሔር ፆምን ሰራልን እንዳንበላም ከለከለን እያሉ ይዋሻሉ፡፡ እግዚያብሔር ፈጣሪያችን ነው፡፡ ግን የምንበላውን ምግባችንን እንድንመገበው ሰጠን እንጂ እርሱን ልናርም አይደለም፡፡
ስለ ሃይማኖቶች መለያየት
ሌላ ትልቅ ምርመራ አለ፡፡ ሰዎች ሁሉ በእግዚያብሔር ዘንድ ትክክል ናቸው፡፡ እርሱም አንድ ህዝብ ለሕይወት አንድ ህዝብ ለሞት አንድም ለምህረት አንድም ለኩነኔ አልፈጠረም፡፡ ይህም አድሎ በስራው ሁሉ ፃድቅ በሆነ በእግዚያብሔር ዘንድ እንደማይገኝ ልቦናችን ያስተምረናል፡፡ ሙሴ ግን አይሁድን ለብቻቸው እንዲያስተምራቸው ተላከ፡፡ ለሌሎች ሕዝቦች ፍርዱ አልተነገረም፡፡ እግዚያብሔር ስለምን ለአንድ ህዝብ ፍርድ ሲነግር ለሌላው አልነገረም፡፡ በዚህ ጊዜ ክርስቲያኖች የእግዚያብሔር ትምህርት  ከኛ ጋር ካልሆነ በስተቀር አይገኝም ይላሉ፡፡ አይሁድና እስላም የህንድ ሰዎችም ሌሎችም ሁሉ እንደነሱ ይላሉ፡፡ እንዲሁ ደግሞ ክርስቲያኖች እርስ በርሳቸው አይስማሙም፡፡ ካቶሊኮች  እግዚያብሔር ከኛ ጋር  ነው ያለ እንጂ ከናንተ ጋር አይደለም ይሉናል፡፡ እኛም እንዲሁ እንላለን፡፡ ሰዎች እንደምንሰማቸው ግን የእግዚያብሔር ትምህርት እጅግ ጥቂቶች ወደሆኑት እንጂ ለብዙዎቹ አልደረሰም፡፡ ከእነዚህ ሁሉ ደግሞ ወደ ማን እንደደረሰ አናውቅም፡፡ እግዚያብሔር ከፈቀደ ቃሉን በሰው ዘንድ ማፅናት ተስኖት ነውን? ሆነም ግን የእግዚያብሔር  ጥበብ በመልካም ምክር ይህ ነገር እውነት እንዳይመስላቸው ሰዎች በሐሰት ሊስማሙ አልተወም፡፡ ሰዎች ሁሉ በአንድ ነገር በተስማሙ ጊዜ ይህ ነገር እውነት ይመስላል፡፡ ሰዎች ሁሉ በሃይማኖታቸው ምንም እንደማይስማሙ በሃሳብም ሊስማሙ አይችሉም፡፡ እስኪ እናስብ ሰዎች ሁሉ ሁሉን የፈጠረ እግዚያብሔር አለ በማለታቸው ስለምን ይስማማሉ? ፍጡር አለ ፈጣሪ ሊገኝ እንደማይችል፤ ስለዚህም ፈጣሪ እንዳለ እውነት ነውና ነው፡፡ ይህ የምናየው ሁሉ ፍጡር እንደሆነ የሰው ሁሉ ልቦና ያውቃል ፡፡ ሰዎች ሁሉ በዚህ ይስማማሉ፡፡ ነገር ግን ሰዎች ያስተማሩትን ሃይማኖት በመረመርን ጊዜ በውስጡ ሐሰት ከእውነት ጋር ተቀላቅሎበታል፡፡ ስለዚህ እርስ በርሱ አይስማማም፡፡ ሰዎች እርስ በርሳቸው አንዱ ይህ እውነት ነው ሲል፡፡ ሁለተኛው አይደለም ሐሰት ነው ሲል ይጣላሉ፡፡ ሁሉም የእግዚያብሔርን ቃል የሰው ቃል እያደረጉ ይዋሻሉ፡፡
እንደገናም የሰው ሃይማኖት ከእግዚያብሔር ብትሆን ክፉዎችን ክፉ እንዲያደርጉ እያስፈራራች መልካም እንዳያደርጉ ትፈቅድላቸው ነበር፡፡ ደጎችንም በትዕግስታቸው ታፀናቸው ነበር፡፡ ለኔም እንዲህ ያለው ሃይማኖት ባሏ ሳያውቅ በምንዝርና  የወለደች ሴትን ትመስለኛለች፡፡ ባሏ ግን ስለመሰለው በሕፃኑ ይደሰታል፡፡ እናቲቱንም ይወዳታል፡፡ በዝሙት እንደወለደችው ባወቀ ጊዜ ግን ያዝናል፡፡ ሚስቱንም ልጅዋንም ያባርራል፡፡ እንዲሁም እኔም ሀይማኖቴን አመንዝራና ዋሾ መሆኑዋን ካወኩ በኋላ ስለርሷ በዝሙት ስለተወለዱ ልጆቿ አዘንኩ ፡፡ እነሱ በጠብ፣ በማሳደድ፣ በመማታት፣ በማሰር፣ በመግደል ወደዚህ ዋሻ ያባረሩኝ ናቸው፡፡ ነገር ግን የክርስቲያን ሃይማኖት እውነት ናት እንዳልል  በዘመነ ወንጌል እንደተሰራ ክፉ አልሆነችም፡፡ የምህረትን ሥራ በሙሉ እርስ በርስ መፋቀርን ታዛለች፡፡ በዚህ ዘመን  ግን የሀገራችን ሰዎች የወንጌልን ፍቅር ወደ ጠብና ሃይል ወደ ምድራዊ መርዝ ለወጡት፡፡ ሃይማኖታቸውን ከመሰረቱ አመፃ እየሰሩ ከንቱ ያስተምራሉ፡፡ በሐሰትም ክርስቲያኖች ይባላሉ፡፡
ስለ አምላክ ህግና ስለ ሰው ህግ
እግዚያብሔር የገዛ ህዝቡን እንዲያስቷቸው ስለምን ዋሾ ሰዎችን ይተዋል ብዮ አሰብኩ፡፡ እግዚያብሔር ግን ለሁሉም ለእያንዳንዱ እውነትንና ሐሰትን እንዲያውቅ ልቦና ሰጥቶናል፡፡ እውነት ወይም ሐሰት እንደፈቃዱ የሚመርጥበት መምረጫም ሰጠው፡፡ እውነትን ብንወድ ለፍጥረት ሁሉ አስፈላጊና ተገቢ የሆነውን እርሱም እንድናይበት እግዚያብሔር በሰጠን  ልቦናችን ውስጥ እንፈልጋት፡፡ ሰው ሁሉ ዋሾ ነውና እውነትንም በሰዎች ትምህርት አታገኟትም፡፡ ከእውነት ይልቅ ሐሰትን ብንመርጥ ስለዚህ እኛ በስህተታችን እንጠፋለን እንጂ ለፍጥረት ሁሉ የተሰራው የፈጣሪ ስርዓትና ሕግ አይጠፋም፡፡ እግዚያብሔር ማንንም በሠራው ሥራ ይጠብቀዋል፡፡ ከሰው ስራ ግን የእግዚያብሔር ስራ ይፀናል፡፡ የሰው ስራ ሊያጠፋው አይችልም ስለዚህም ከጋብቻ ይልቅ ምንኩስናን ይበልጣል ብለው የሚያምኑ እነርሱ በፈጣሪ ስራ ፅናት ወደ ጋብቻ ይሳባሉ፡፡ ፆም ነፍስ እንደሚያፀድቅ  የሚያምኑ እነርሱ ደግሞ እረሃብ በበዛባቸው ጊዜ ይበላሉ፡፡ ገንዘቡን የተወ ፍፁም እንዲሆን የሚያምኑ በገንዘብ ለሚያገኙት  ጥቅም ወደ ገንዘብ መፈለግ ይሳባሉ፡፡ ብዙዎች የሀገራችን መነኩሴዎችም እንደሚደርጉት ከተውት በኋላ እንደገና ይፈልጉታል፡፡ እንደዚሁ ዋሾዎች ሁላቸው የተፈጥሮን ሥራ ሊያፈርሱ ይፈልጋሉ፡፡ ነገር ግን ደካማነታቸውን ያሳያሉ እንጂ አይችሉም፡፡ ፈጣሪም ይስቅባቸዋል፡፡ የፍጥረት ጌታም በላያቸው ይሳለቅባቸዋል፡፡ እግዚያብሔር የእግዚያብሔርን ፍርድ ማድረግ ያውቃልና ሃጥአንም በእጁ ሥራ ወጥመድ ተጠመደ፡፡ ስለዚህም የጋብቻን ሥርዓት የሚያስነውር መነኩሴ በክፉ በሽታና ፍጥረቱ ባልሆነ በሌላ የሴት አበሳ በዝሙት ተፅኖ ይጠመዳል፡፡ ገንዘባቸውን የሚንቁ ገንዘብ እንዲያገኙ በሀብታሞችና በነገስታት ዘንድ ግብዞች ይሆናሉ፡፡ ለእግዚያብሔር ብለው ዘመዶቻቸውንም በሽምግልናቸው በችግራቸው እረዳት ባጡ ጊዜ የተው በነሱ ሽምግልና ጊዜ ሰውና እግዚያብሔርን ወደ ማማት መሳደብ ይደርሳሉ፡፡ እንደዚሁም የፈጣሪን ሥርዓት  የሚያፈርሱ ሁሉ በእጃቸው  በሰሩት ወጥመድ ይወድቃሉ፡፡ እንደገናም እግዚያብሔር ክፋትን ስህተትን በሰው መካከል ይተዋል፡፡ ነፍሶቻችን በዚህ ዓለም የእግዚያብሔር  ጥበብ የፈጠረውን የፈተና ቀን ይኖራሉ፡፡
ጠቢቡ ሰለሞን
"እግዚያብሔር ፃድቃንን ፈተናቸው፡፡ ወርቅ በእሳት እንደሚፈተን ይፈትናቸዋል፡፡ ለእርሱ የተዘጋጁ ሆነውም አግኝቷቸዋልና፡፡ እንደተወደደ ዕጣን መአዛም ይቀበላቸዋል" ይላል፡፡    
ከሞታችን በኋላም ቢሆን ወደፈጣሪያችን በገባን ጊዜ እግዚያብሔር በእውነትና በትልቅ በጥበብ ከሠራው ሁሉ እውነትና ቅን የሆነውን መንገድ ሁሉ እንለያለን፡፡ ነፍሳችንም ከስጋዊ ሞታችን በኋላ እንደምትድን ይታወቃል፡፡ በዚህ ዓለም ውዴታችን አይፈፀምምና የሌላቸው ይፈልጋሉ ያላቸው ባላቸው ላይ እንደገና ሊጨምሩ ይፈልጋሉ፡፡ ሰው በዚህ ዓለም ያለው ሁሉ እንኳን ቢኖረው እንደገና ይወለዳል እንጅ አይጠግብም፡፡ ይህም የፍጥረታችን ጠባይ ለሚመጣው ንብረት እንጅ ለዚህ ዓለም ንብረት ብቻ እንዳልተፈጠርን ያመለክታል፡፡ በዚያውም የፈጣሪያቸውን ፈቃድ የፈፀሙ ነፍሳት ፍፁም ይጠግባሉ እንጅ ከእንግዲህ ሌላ አይወዱም፡፡ አለዚያ ግን የሰው ፍጥረት አስፈላጊውን ሁሉ አላገኝምና ጎዶሎ በሆነ ነበር፡፡ እንደገናም ነፍሳችን እግዚያብሔርን ማሠብ ትችላለችና በሃሳቧም ታየዋለች፡፡ እንደገናም ለዘላለም መኖር ማሰብ ትችላለች፡፡ እግዚያብሔርም ይህን ማሰብ በከንቱ አልሰጣትም፡፡ ነገር ግን እንደሰጣት ልታስብና እንድታገኝም ሰጣት፡፡ ደግሞ በዚህ ዓለም ፅድቅ ሁሉ አይፈፀምም፡፡ ክፉ ሰዎች ከዚህ ዓለም መልካም ይጠግባሉ፡፡ ደጋጎች ይራባሉ፡፡ እሚደሰት ክፉ አለ፣ እሚያዝን ደግ አለ፣ እሚደሰት አመፀኛ አለ፣ እሚያለቅስ ፃድቅም አለ፣ ስለዚህም ከሞታችን በኋላ ለሁሉ እንደየምግባሩ እሚከፍለው ሌላ ኑሮና ፍፁም ፅድቅ ያስፈልጋል፡፡ በብርሀን ልቦናችን ተገለፀላቸው፡፡ የፈጣሪን ፈቃድ የፈፀሙና በተፈጥሯቸውም ፀባያዊ ህጉን የጠበቁ ዋጋቸው ይከፈላቸዋል፡፡ የተፈጥሮን ህግ ከመረመርን የተረጋገጠ መሆኑን ልቦናችን በግልፅ ይነግረናል፡፡ ነገር ግን ሰዎች ሊመረምሩ አልፈለጉምና የፈጣሪያቸውን ፈቃድ በእውነት ከመፈለግ የሰዎችን ቃል ማመን መረጡ፡፡
ስለ ባህሪያዊ ዕውቀት
 የፈጣሪ ፈቃድ ግን ለእግዚያብሔር ለፈጣሪ ስገድ ፣ ሰውንም ሁሉ እንደነፍስህ አፍቅር ይላል፡፡ ይህ በልቦናችን እውነት መሆኑ ይታወቃል፡፡ እንደገናም በልቦናችን እውነትነቱ የሚታወቅ ሌላ እውነት "ሊያደርጉብህ የማትፈልገውን በሰው አታድርግ፡፡ ላንተ ሊያደርጉልህ የምትፈልገውን አድርግላቸው" ይላል፡፡ የሰንበትን ማክበር የሚለው ካልሆነ በቀር አስሩ የኦሪት ትዕዛዛት የፈጣሪ ናቸው፡፡ ሰንበትን ለማክበር ግን ልቦናችን ዝም ይላል፡፡ ልንገድልና ልንሰርቅ፣ ልንዋሽና የሰው ሚስት ልንሰርቅ ይህን የሚመስለውን ልናደርግ እንደማይገባን ልቦናችን ይነግረናል፡፡ እንዲሁ ስድስቱ የወንጌል ቃላት የፈጣሪ ፈቃዶች ናቸው፡፡ እኛ ይህን የምህረት ስራ ሊያደርጉልን እንፈልጋለን፡፡ በሚቻለን ለሌሎች ልናደርግላቸው ይገባናል፡፡ ደግሞም በዚህ ዓለም ሕይወታችን፣ ንብረታችን እንድንጠብቅ የፈጣሪ ፈቃድ ነው፡፡ ከፈጣሪ ፈቃድ ወጥተን በዚህ ሕይወት እንኖራለን፡፡ በተቀደሰ ፈቃዱ ካልሆነ በቀር ልንተወው አይገባንም፡፡ እርሱ ፈጣሪያችን ለሁሉ ልቦናና ችሎታ ስለሰጠ ኑሯችንን በዕውቀትና በሥራ እንድናሳምረው ይፈቅድልናል፡፡ ይህ ካልሆነ በቀር የሕይወታችን ፍላጎት አይገኝም፡፡ እንዲሁ አንዱ ካንዷ ጋር መጋባትና ልጆች ማሳደግን ፈቅዷል፡፡ ደግሞም ከልቦናችን ጋር የሚስማማ ለህይወታችንም ለሁሉም የሰው ልጆች ኑሮ የሚያስፈልጉ ሌሎች ብዙ ሥራዎች አሉና የፈጣሪ ፈቃድም እንዲሁ ስለሆነ ልንጠብቀው ይገባናል፡፡ እግዚያብሔር ፍፁማን አድርጎ እንዳልፈጠረን ልናውቅ ይገባናል፡፡ ለመፈፀማችን የተዘጋጀን አዋቂዎችና በዚህም ዓለም እስካለን ድረስ እንድንፈፅምና ፈጣሪያችን በጥበቡ ላዘጋጀልን ዋጋ የተዘጋጀን እንድንሆን አድርጎ ፈጠረን፡፡ በዚህ ምድር ፍፁማንና ብፁዓን አድርጎ ሊፈጥረን ለእግዚያብሔር ይቻለው ነበር፡፡ ነገር ግን ለመፈፀማችን እምንዘጋጅ አድርጎ ፈጠረን እንጅ እንዲሁ ሊፈጥረን አልፈቀደም፡፡ ከሞታችን በኋላ ፈጣሪያችን ለሚሰጠን ዋጋ የተዘጋጀን ፍፁማን እንድንሆን በዚህ የፈተና ዓለም መካከል አኖረን፡፡ በዚህ ዓለም እስካለንም ወደ እርሱ እስኪወስደን ድረስ እየታገስን ፈቃዱን እየፈፀምን ፈጣሪያችን ልናመሰግነው ይገባል፡፡ የፈተናችንንም ጊዜያቶች እንዲያቀልልን ባለማወቃችን ሠራነውን የእብደት አበሳ እንዲተውልን የተፈጥሮ ሕግጋትን አውቀን እንድንጠብቃቸው ልቦና እንዲሰጠን ወደቸርነቱ እንለምን፡፡ ፀሎት ደግሞ ላዋቂ ነፍስ አስፈላጊ ነውና ዘወትር ልንፀልይ ይገባናል፡፡ አዋቂ ነፍስ ሁሉን የሚያውቅና ሁሉን የሚጠብቅ ሁሉን የሚገዛ እግዚያብሔር እንዳለ ታውቃለች፡፡ ወደ እርሱ እንድትፀልይም ከእርሱ መልካም እንድትለምን፣ ከክፉ እንድትድንና ሁሉን ወደ ሚችል እጅ እንድትማፀን ወደ እርሱ ትሳባለች፡፡ እግዚያብሔር ምሁርና ትልቅ ነው፡፡ የሚሳነውም የለም፡፡ ከበታቹ ያለውን ያያል፣ ሁሉንም ይይዛል፣ ሁሉን ያውቃል ፣ ሁሉን ይመራል፣ ሁሉን ያስተምራል አባታችን ፈጣሪያችን ጠባቂያችን ነው፡፡ የነፍሳችን ዋጋ ቸርና ይቅር ባይ ችግራችንን ሁሉ የሚያውቅ ነው፡፡ ለሕይወት እንጂ ለጥፋት አልፈጠረንም፡፡ በትዕግስታችን ይደሰታል፡፡
ጠቢቡ ሰለሞን
"ጌታ ሆይ አንተ ከሁሉ በላይና ቻይ ነህና ሁሉን ታስተምራለህ፣ ሰዎችን ለንስሃ ታቆያቸዋለህ፣ ሃጢያታቸውንም ችላ ትለለህ፣ አንተም ያደረከውን ሁሉ ምንም የምትንቀው ስለማይኖር ሁሉን ትወዳለህ፡፡ በሁሉ ፍጥረት ላይም ትራራለህ ይቅር ትላለህ" ይላል፡፡
 የእግዚያብሔርም ታላቅነቱን እንድናስብ ለስጋችንና ለነፍሳችን እሚያስፈልገንን ለማግኝት ወደ እርሱ እንድንፀልይና እንድናመሰግነው አዋቂዎች አድርጎ ፈጠረን፡፡ ይህም ሁሉ በሰው ልብ ያገባ ፈጣሪያችን ዕውቀት ያስተምራልና እንዴትስ ሀሰት ሊሆን ይችላል፡፡
ስለ ፈተናና ፀሎት
እኔም እነደገና በሙሉ ልባችን በፍቅርና በዕምነት በትዕግስትም ወደ እርሱ በፀለይን ጊዜ እግዚያብሔርም ፀሎታችንን እነደሚሰማ በሌላ መንገድ አወኩ፡፡ እኔ በልጅነት ጊዜየ ስለ እግዚያብሔር ሥራ ምንም ሳላስብ ወደ እርሱ ስፀልይ ሃጢያተኛ ነበርኩ፡ ፡ለአዋቂ ፍጥረት የማይገባ ብዙ በደል በደልኩ፡፡ ስለሃጢያቴም ሰው ከእርሱ ሊያመልጥ ወደማይችለው ወጥመድም ወደኩ፡፡ ፈፅሜ ልጠፋም ቀረብኩ፡፡ የሞት ፍርሃትም መጣብኝ፡፡ የዚያን ጊዜ ወደ እግዚያብሔር ተመልሼ እርሱ የማዳንን መንገድ ያውቃልና እንዲድነኝ ብየ ወደ እርሱ መፀለይ ጀመረኩ፡፡ እግዚያብሔር ጌታ ሆይ ለሃጢያቴ እፀፀታለሁ ፈቃድህንም ለማድረግ እፈልጋለሁ አልኩ፡፡በሙሉ ልቤም ብዙ ጊዜ ፀለይኩ እግዚያብሔር ሰማኝና ፈፅሞ አዳነኝ፡፡ ወደ እርሱ ተመልሼም በፍፁም ልቤ አመሰገንኩት፡፡
በመዝሙረ ዳዊት "እግዚያብሔር  የልመናየን ቃል ሰምቷል ወደድኩት" የሚለውንም ዘመርኩ፡፡ ደገምኩት፡፡ ይህም መዝሙር ስለኔ የተፃፈ መሰለኝ፡፡ እንደገናም ልድን ካልሆነ በስተቀር አልሞትም፡፡ የእግዚያብሔርንም ሥራ እነግራለሁ አልኩ፡፡ ነገር ግን ዘወትር ወደ ንጉስ የሚያሳጡኝ ነበሩ፡፡ ይህ ሰው ጠላትህ ነው ፤ ለፈረንጆቹም ጠላታቸው ነው ይሉታል፡፡ የንጉሱም ቁጣ በላየ እንደተቃጠለ አወኩ፡፡ አንድ ቀንም የንጉሱ መላክተኛ መጥቶ ንጉሱ ፈጥነህ ወደ እኔ ና ይልሃል አለኝ፡፡ እኔም እጅግ ፈራሁ፡፡ የንጉስ ሰዎች ስለሚጠብቁኝም ልሸሽ አልቻልኩም ባዘነ ልቤም ሌሊት በሙሉ ፀለይኩ፡፡ ሲነጋም ተነስቼ ሄጄ ወደ ንጉሱ ገባሁ፡፡ እግዚያብሔርም የንጉሱን ልብ ስላራራው በፍቅር ተቀበለኝ፡፡ ስለፈራሁት ነገርም ምንም አላለኝ፡፡ ነገር ግን ስለትምህርትና የመፅሃፍት ነገር ጠየቀኝ፡፡ አንተ የተማርክ ሰው ነህ፤ እነርሱም በጣም የተማሩ ናቸው፡፡ ፈረንጆቹን ትወዳቸው ዘንድ ይገባሀል አለኝ፡፡ ስለፈራሁትም እሺ ፈረንጆቹ በእውነት የተማሩ ናቸው አልኩት፡፡ ከዚህም በኋላ ንጉሱ አምስት ወቄት ወርቅ ሰጥቶ በሰላም ሰደደኝ፡፡ ከንጉሱ ወጥቼ እተደነቅኩ ለኔ መልካም ስላደረገልኝ እግዚያብሔርን አመሰገንኩት፡፡ እነደገናም ወልደ ዪሃንስ ባሳጣኝ ጊዜ ልሸሸው ስለተቻለኝ እንደፊተኛው እንዲያድነኝ ሳልፀልይ ሸሸሁ፡፡ ሰው እግዚያብሔርን በከንቱ ሳይፈታተነው የሚቻለውን ሁሉ ሊያደርግ ይገባል፡፡ አሁን ግን ስለሸሸሁና በዋሻየም ስለሁንኩ ቀድሞ ያላሰብኩትን እንዳስብና ለነፍሴም ትልቅ ደስታ እሚያስደስታት እውነትን እንዳወኩ፣ ወደ ፈጣሪየ የመመለስ ፍፁምነት ምክንያት ስላገኝሁ ፈጣሪየን አመሰገንኩ፡፡ ፍርድህን እንዳውቅ ያሳመምከኝ ይገባኛል፡፡ ከመምህራን ጋር  በነበረኩ ጊዜ ካስተዋለኩት ይልቅ ብቻየን በዋሻየ ሆኞ በጣም አስተውያለሁና፡፡ ይህም የፃፍኩት እጅግ ትንሽ ነው፡፡ ይህን የመሳሰሉትን ብዙ እያሰብኩ በዋሻየ ቆየሁ፡፡ እግዚያብሔርም የፍጥረታቱን ምስጢር ለማወቅ ጥበብ ስለሰጠኝ አመሰገንኩት፡፡ ነፍሴም የእግዚያብሔርን ጥበብ ሥራ ከማሰብ በቀር ሁሉን እየናቀች ወደ እርሱ ትሳብ ነበር፡፡ በሰፊው ልቤም በዳዊት መዝሙር ሁልጊዜ እፀልይ ነበር፡፡ ይህ ፀሎት  በጣም ይጠቅመኛልና ሕሊናየንም ወደ እግዚያብሔር ያነሳሳልኛል፡፡ በመዝሙረ ዳዊት ከሕሊናየ ጋር የማይስማማ ባገኝሁ ጊዜ እኔ ተርጉሜ በዕውቀቴ አስማማዋለሁ፡፡ ሁሉም ያምርልኝ ነበር፡፡ እንደዚህ እያልኩ በፀለይኩም ጊዜ በእግዚያብሔር መታመኔ ይጨምር ነበር፡፡ ሁልጊዜም እንደዚህ እል ነበር፡፡
"ጌታ ሆይ ፀሎቴን ስማኝ፡፡ ልመናየንም ችላ አትበል፡፡ ከሰው ልጆች ግፊትም አድነኝ፡፡ ጌታ ሆይ ይቅርታህን ከኔ አታርቅ፡፡ ምህረትህም፣ ፅድቅህም ዘወትር ያግኙኝ፡፡ ጌታ ሆይ ምኞቴን ሁልጊዜ እንድትሰጠኝም አልፈር፡፡  እንዲሁም እያልኩ ስምህን ለዘላላም እዘምራለሁ፡፡ ወደ እኔ ተመልከትና ይቅር በለኝ፡፡ ለባሪያህ ሃይል ስጠው፡፡ የደህንነት ምልክት ከኔ ጋር አድርግና የባሪያህንም ልጅ አድነው፡፡ ስለስምህም ምራኝና መግበኝ፡፡ ነፍሴን ከሃጢያን ጋር አትሳባት፡፡ ምህረትህም ከበላየ ትሁን፡፡ ባንተ ላይ ታምኛለሁና በንጋት እሚሰማ ምህረትን አድርግልኝ፡፡ በምድር ላይ ብፁዕ አድርገህ ጠብቀኝ፡፡ በጠላቶቼም እጅ አታግባኝ፡፡ ከተስፋየ አታሳፍረኝ፡፡ ተድላና ደስታ አሰማኝ፡፡ እነርሱ ይገረማሉ አንተ ግን ባርክ፡፡ ይህም በጅህ እንደሆነ አወኩ፡፡"
ይህንንና የሚመስለውን በሙሉ በልቤ ቀንና ሌሊት እፀልይ ነበር፡፡ ስለፀሎት ስጋዊና መንፈሳዊ ሥራ ጠዋትና ማታ የምፀልየው ፀሎትም እንዲህ ነበር፡፡
"ፈጣሪየና ጠባቂየ ሆይ እሰግድልሀለሁ በሙሉ ልቤም እወድሀለሁ በዚች ለሊትም ላደረክልኝ መልካምም አመሰግንሀለሁ፡፡ ሲነጋም በዚች ቀን ጠብቀኝ እልሀለሁ፡፡ ሲመሽም በዚችኛዋ ለሊት በዚችኛዋ ቀንና  በሕይወቴ ዘመን ሁሉ ፈቃድህን በእኔ ላይ እንዳውቀውና እንድፈፅመው አዋቂ አድርገኝ፡፡ ሃጢያቴንም ይቅር በለኝ፡፡ ለሕይወቴ የሚያስፈልገኝንም የሚበቃኝን ሁልጊዜ ስጠኝ፡፡ አንተን በመታመን ዘወትር አፅናኝ ጌታየ ሆይ ስለቸርነትህና ስለሃይልህ ስለታላቅነትህም ከሰው ምላስና  እጅ፣ ከድህነትና ከደዌ ስጋ፣ ከነፍስ ሃዘንም አድነኝ፡፡ ደግሞም ባንተ ታመንኩ" የሚለውን በመዝሙር ያለውን እፀልይ ነበር፡፡
 እንደገናም ፀሎት ብቻውን አይጠቅመኝምና ለህይወቴ የሚያስፈልገኝን በተቻለኝ ሁሉ ልሰራና ልደክም ይገባኛል ብየ አሰብኩ፡፡ ነገር ግን ስራ አላውቅምና በእግዚያብሔር ሃይል እገባለሁ፡፡
"ጌታ ሆይ ስራየም አለበረከትህ ምንም አይጠቅመኝም፡፡ ሃሳቤን፣ ኑሮየን፣ ሥራየን አንተ ባርከው፡፡ አንተ በምታውቀው መንገድ ደስታንና ገንዘብን ስጠኝ፡፡ከኔ ጋር በሥራ ያሉ ሰዎችን ልብ ወደ መልካም መልስልኝ፡፡ ሁሉ በተባረከው ፈቃድህ ይሆናልና ለኔም የሽምግልናየን ጊዜ አሳምርልኝ፡፡"
ልባችን ዘወትር በእግዚያብሔር እጅ እንደሆነ አወቅኩ፡፡ በበሽታና በድህነት በችግርም መካከል ብንኖር እግዚያብሔር ብፁአንና ደስተኞች ሊያደርገን ይችላል፡፡ እነደገናም በዚህ አለም በሃብትና በደስታ ሁሉ መካከል ብንኖር ጎስቋሎች ሊያደርገን ይችላል፡፡ ስለዚህም ድሆችና ችግረኞች በልባቸው ደስታ ሁልጊዜ ሲጫወቱ እናያለን፡፡ ሀብታሞችና ነገስታትም በምኞታቸው ብዛት በሀብታቸው መካከል ሲያዝኑና ሲጎሳቆሉ እናያለን፡፡ እኛ ሳናውቀውና ሳንፈልገው የመነሻ ምክንያቱን ሳናውቅ ሀዘን በልባችን ውስጥ ይመጣል፡፡ በምድር ብፁኣን እንዲያድርገንና ፍስሃና ደስታ እንዲሰማን ወደ እግዚያብሔር ልንፀልይ ይገባናል፡፡ እግዚያብሔር ለፃድቃን ብርሃን፣ ልባቸው ለቀና ደስታን ይሰጣቸዋል፡፡ እርሱ ያውቃልና የልባችንንም መንገድ ሁሉ ይገዛል፡፡ እርሱ በችግራችን ደስተኞች በድሎታችንም ሀዘንተኞች ሊያደርገን ይችላል፡፡ እግዚያብሔር እሚሰማን እንጂ ለሰዎች እንደሚመስላቸው በደስታና ሀዘን አይደርሰንም፡፡ አንተ ፈጣሪየና ጌታየ በምድር እስካለህ ድረስ ብፁዕ  አድርገኝ  ደስታና  ትፍስህትንም  አሰማኝ፡፡ ከሞቴ በኋላም ወደ አንተ ወስደህ ከአንተ አስጠጋኝ አልኩ ፡፡ እንዲህ ብየ ቀንና ለሊት እየፀልይኩ እግዚያብሔርን ስነ ፍጥረትን፣ እንስሳትን፣ የበርሃ አራዊትን በየስርዓታቸው እያደነቅሁ ነበር፡፡ እነሱ ግን ሕይወታቸውን ለመጠበቅና ዘራቸውን ለማራባት በፀባየ ተፈጥሯቸው ይሳባሉ፡፡ እንደገናም የበረሃ እንጨትና ሣር በትልቅ ጥበብ የተፈጠሩ ይበቅላሉ፣ ይለመልማሉ፣ ያብባሉ በየወገኖቻቸውም የዘራቸውን ፍሬ አለ ስህተት ያወጣሉና ነፍስ ያላቸው ይመስላሉ፡፡ እንደገናም ተራሮችና ኮረብቶች ፣ ወንዞችና የውሃ ምንጮች  ሥራ ሁሉ ስምህን ያመሰግነዋል፡፡ጌታየ ሆይ ስምህን በሁሉ በሰማይ እና በምድር እጅግ ተመስግኗል፡፡ ይህ የእጅህ ስራ ፀሀይ የብርሀንና የዓለም ህይወት ምንጭ እጅግ ትልቅ ነው፡፡ አንተ የሰራሃቸውን፣ የመሰረትካቸውን ጨረቃና ከዋክብትን አንተ ከሰራህላቸው መንገድ ሌላ አለመዛነፋቸው በጣም ያስደንቃሉ፡፡ በመራቃቸው ደቃቃዎች የሚመስሉ ከዋክብትን ቁጥራቸውን፣ እርቀታቸውን፣ ታላቅነታቸውንስ የሚያውቅ ማነው? ደመናዎችም ልምላሜን ለማብቀል ውሃዎች ያፈሳሉ፡፡ ይህ ሁሉ ታላቅና እጅግ የሚያስደንቅ ጥበብ በጥበብ የተፈጠረ ነው፡፡ እንደዛም ብየ ፈጣሪየን እያደነኩና ፈጣሪየን እያመሰገንኩ ሁለት ዓመት ተቀመጥኩ፡፡
እንደገናም የእግዚያብሔር ስራ እጅግ መልካም ነው፡፡ ሀሳቡም ትልቅና የማይነበብ ነው ብየ አሰብኩ፡፡ እንግዲያስ ትንሹና ምስኪኑ ሰው ለሰው ጥበቡንና እውነቱን እንደገለፀለት ከእግዚያብሔር ዘንድ ተልኬ መጣሁ እያለ ስለምን ይዋሻል? ፈጣሪ ታላቅነቱን እንድናውቅ ከሰጠን ህሊና ይልቅ እጅግ ዝቅ ያለና የተናቀ ግዑዝ ባህሉን ካልሆነ በቀር ሊገልፅልን አይችልም፡፡ ጌታ ሆይ እኔ በፊትህ ደህና ምስኪን ነኝ፡፡ ስላንተ የማይገናኝን እንዳውቅና ታላቅነትህን እንዳደንቅ አዲስ ምስጋና ሁልጊዜ እንዳመሰግንህ ልቦና ስጠኝ፡፡
የዘርዓ ያዕቆብ ወደ እንፍራንዝ መግባት
በ1625 ዓ/ም ሱስንዮስ ሞቶ ልጁ ፋሲለደስ ነገሰ፡፡ እርሱም በመጀመሪያ ፈረንጆቹን ወደደ፡፡ ግብፃዊያንንም አላባረራቸውም በዚህ ምክንያት በኢትዮጵያ ሁሉ ሰላም ሆነ፡፡ የዚያን ጊዜ ከዋሻየ ወጥቼ መጀመሪያ ወደ አማራ አገሮች ሄድኩ፡፡ ኋላም ወደ በጌምድር ተመለስኩ ለሁሉም በፈረንጆች ጠላትነት በሱስንዮስ ዘመን ከተባረሩት መነኮሳት አንዱ መሰልኳቸው ፡፡ ስለዚህም ወደዱኝና ምግብና ልብስም ሰጡኝ፡፡ በዚህ ሁኔታ ከአገር ወደ አገር ስመላለስ የካህናቶቿን ክፋት አውቃለሁና ወደ አክሱም መመለስን አልወደድኩም፡፡ ሰው የሚሄድበት ከእግዚያብሔር እንደሚታዘዝ አሰብኩ፡፡ ጌታ ሆይ የምሄድበትን መንገድና የምኖርበትን ነገር ምራኝ አልኩት፡፡ ወደጎጃም ምድር ተሻግሬም ለመኖር አሰብኩ፣ ነገር ግን እግዚያብሔር ወደአላሰብኩት መራኝ፡፡ አንድ ቀን ወደ እንፍራንዝ አገር ወደ አንድ ጌታ ሰው የእግዚያብሔር ሀብት ነውና ሀብቱ ወደ ተባለ ደረስኩ በዚያውም አንድ ቀን አደርኩ፡፡ በማግስቱም አክሱም ወዳሉት ዘመዶቼ ደብዳቤ እንድልክ ከእርሱ ቀለምና ወረቀት ለመንኩት፡፡ ይህ ሰውም
 "አንተ ፀሀፊ ነህ ወይ?" አለኝ
 "አዎ ፀሀፊ ነኝ" አልኩት
 "ከኔ ጋር ጥቂት ቀን ተቀምጠህ የዳዊት መዝሙርን ፃፍልኝና ዋጋህን እሰጥሀለሁ" ብሎ ተናገረኝ
"እሺ" አልኩት፡፡
የድካሜንም ፍሬ የምመገብበትን መንገድ ስላሳየኝ እግዚያብሔርን በልቤ አመሰገንኩት፡፡ እውነት ባስተምር ሰዎች ሊጠሉኝና ሊከሱኝ፣ ሊያባርሩኝ ካልሆነ አይሰሙኝምና ወደ ቀድሞ ሊቅነቴ ተመልሼ ሐሰትን ማስተማር ጠላሁ፡፡ እኔ ግን ከሰው ሁሉ ጋር በፍቅርና በሰላም መኖርን ወደድኩ፡፡ በሃጥአን ቤት ከብሬ ከምኖር ግን ከሰው ተለይቼ የድካሜን ፍሬ እየተመገብኩ እግዚያብሔር በሰጠኝ  ጥበብ ተሸሽጌ አልባሌ መስየ መኖርን መረጥኩ፡፡ በጥቂት ጊዜም ቀለምና ብራና አዘጋጅቼ አንድ የዳዊት መዝሙር ፃፍኩ፡፡ ፅህፈቴም ያማረች ናትና ጌታዮ ሀብቱና ሁሉም አይተዋት ተደነቁ፡፡ ጌታዮ ሀብቱም ደሞዜን አንድ መልካም ልብስ ሰጠኝ ፤ ደግሞም ወልደ ሚካኤል የተባለ የጌታየ ሀብቱ ልጅ  ላባቴ እንደፃፍከው ለእኔም ፃፍልኝ አለኝና ፃፍኩለት፡፡ አንድ በሬና ሁለት ፍየሎችም ሰጠኝ፡፡ ከዚህ በኋላ ብዙዎች ወደ እኔ ዘንድ መጥተው ዳዊትና ሌሎች መፅሐፍትን፣ ደብዳቤዎችን አፃፉ፡፡ በዚያ አገር ካለ እኔ በቀር ሌላ ፀሐፊ አልነበረምና ልብስ፣ ፍየሎች፣ እህል፣ ጨውና ሌላም እነርሱን የመሳሰሉ ሰጡኝ፡፡ ለጌታየ ሀብቱም አንድ ወልደ ገብርኤል ተሰማ የተባለና ሁለተኛ ወልደ ህይወት ምትኩ የተባሉ ሁለት ልጆች ነበሩት፡፡ አባታቸው ሀብቱም የሚበቃህን ምግብ እሰጥሃለሁና  በእጅህ ፅፈህ የምታፈራውን  ላንተ ይሆናልና፤ የዳዊትን ንባብ አስተምራቸው አለኝ፡፡ አባቴ ሆይ ያዘዝከኝን ሁሉ አደርጋለሁ አልኩት፡፡ ነገር ግን ካንተ በቀር ዘመድ የለኝምና በአባቴና በእናቴ ዘመዶችም ፋንታ ዘመድ ሁነኝ አልኩት፡፡
ስለ ሕጋዊ የፈቃድ ጋብቻ
ይህ መንገድ ወደ አበሳ ይስባልና ሴት የሌላቸው ወንድ ብቻውን ይኖር ዘንድ እንደማይገባው አወኩ፡፡ ለፊተኞቹ ሴት ታስፈልጋቸዋለች እንጅ ወንድ ብቻውን ይኖር ዘንድ መልካም አይደለም፣ እንደተባለው በሰሩት ወጥመዳቸው እንዳይጠመዱ ሰዎች ተፈጥሯቸውን ክደው ሊኖሩ አይገባቸውም፡፡ ጌታየ ሀብቱም የዘመኑን ክፋት ፈርቼ መሰልኩ እንጂ መነኩሴ አይደለሁም አልኩት፡፡ ለጌታየም ሂሩት የተባለች አንዲት ቤተሰብ ነበረች፡፡ ምግባረ መልካምና ልባም፣ ትዕግስተኛ እንጂ ደም ግባታም አይደለችም፡፡ ጌታየ ሀብቱም
"ይህች ልጅ ሚስት እንድትሆነኝ ስጠኝ" አልኩት
"እሺ ከእንግዲህ ባሪያህ እንጂ ባሪያየ አይደለችም፡፡"
"ሚስቴ ካልሆነች በስተቀር ባሪያየ አይደለችም፡፡ ወንድና ሴት በጋብቻ በአንድ ስጋና በአንድ ንብረት ትክክል ናቸው እና ጌታና ባሪያ ልንላቸው አይገባም፡፡"
ጌታየ ሀብቱ "አንተስ የእግዚያብሔር ሰው ነህና እንደ ፈቃድህ አድርግ" አለኝ፡፡ ያቺንም ልጅ ጠራናት፡፡
 እኔም "ሚስቴ ልትሆኝ ትወጃለሽን" አልኳት
"ጌታየ እንደፈቀደ" አለችኝ ፡፡
ጌታየ ሀብቱም "እኔስ እፈቅዳለሁ" አላት፡፡
እርሷም "ከአንተ እሚበልጥ የት አገኛለሁ መልካም" አለችኝ፡፡ ጌታየ ሀብቱም
"አባታችን ሆይ ባርከን አልነው፡፡"
"እግዚያብሔር ይባርካችሁና ይጠብቃችሁ፡፡ ለረዥም ጊዜ ፍቅርና ጤና ይስጣችሁ፡፡ ክፉ ነገርን ከእናንተ አርቆ በዚህ አለም ጥሪት ጋር ልጆች ይስጣችሁ" አለን፡፡
"አሜን" አልን፡፡
ይህችም ሂሩት ሚስቴ ሆነችና በጣም ወደደችኝ፡፡ በጌታየ ሀብቱ ቤት የተናቀች ነበረችና፣ ቤተሰቦቹም ዘወትር ያሳዝኗት ስለነበሩ ዛሬ በጣም ተደሰተች፡፡ እኔም ስለወደደችኝ በተቻለኝ ሁሉ እንዳስደስታት በልቤ ወሰንኩ፡፡ እንደኛ ጋብቻ ከእግዚያብሔር የተባረከና በፍቅር የፀና ሌላ ጋብቻ እሚገኝ አይመስለኝም፡፡ ከአክሱም  በሸሸሁ ጊዜ ከእኔ ጋር የወሰድኩት የቀረኝ ሁለት ወቄት ወርቅ ነበረኝ፡፡ በእጅ ፅህፈቴም ከብቶችና ፍየሎች ፣ ልብስም አፈራሁ፡፡ በጌታየ ሀብቱ ጎረቤትም ትንሽ ቤት ሰራሁ፡፡ ከዚያም ከሚስቴ ጋር በፍቅር ነበርኩ፡፡ እኔ እየፃፍኩ የጌታየን የሀብቱን ልጆች ሳስተምር እርሷም ቀንና ሌሊት ትፈትል ነበር፡፡ ጌታየ ሀብቱም ልጆቹን ስላስተማረኩለት በየወሩ አንድ እንስራ ጤፍ ይሰጠኝ ነበር፡፡ እንዲህ ብየም ከሚስቴ ጋር በፍቅርና በመልካም ኑሮ አራት አመት ኖርኩ፡፡ በ1631 ዓ.ም ጥቅምት 11 ሰኞ ቀን ወንድ ልጅ ወለደችና በልጃችን ተደሰትን፡፡ በፀጋ አባቴ በሆነው ሰምም ሀብተ እግዚያብሔር ብየ ሰየምኩት፡፡ ከሦስት ዓመት በኋላም አቡነ አልፎንዝ ወደ ሀገሩ ሄደ፡፡ ጠላቶቼም ሁሉ ተነሱ፡፡ ወዳጆቹ ከእርሱ ጋር ተሰደዱ፡፡ በዚያን ጊዜም የጥንት ትምህርት የሚያስተምሩ መምህራኖች በሀገር ሁሉ ተፈለጉ በአክሱም ያሉት ዘመዶቼም እንደቀድሞው በአክሱም ሆኝ ወደ ሊቅነቴ ተመልሼ መፅሃፍትን እንዳስተምር ፈለጉኝ፡፡ በአቡነ አልፎንዝ ጊዜ የነበረውን ስደት ፈርቼ የሸሸሁ ስለመሰላቸው ጠላቶችህ ጠፍተዋልና ወዳጆችህ ድነዋልና ወደ እኛ ተመለስ ብለው መልክተኞች ላኩብኝ፡፡ እኔም ጠላት የለኝም፡፡ ይህ የእግዚያብሔር ሰው ጌታየ ሀብቱና ልጆቹ ሚስቴም ካልሆኑ በቀር ወዳጅ የለኝም፡፡ ከቶም ልተዋቸው አልችልምና ለኔ ወደ እናንተ መመለስ አይሆንልኝም እናንተም በሰላም ኑሩ ብዮ መለስኳአው፡፡ ይህም ግብዝ ጠላቴ መጀመሪያ ወደ ንጉስ ሱስንዮስ ያሳጣኝ ጠላቴ ወልደ ዩሐንስ አቡነ አልፎንዝ ከሄደ በኋላ ወደ ግብፃዊያን ሃይማኖት ተመለሰ፡፡ ነገር ግን ለጊዜው የሚመቸው ካላሆነ በስተቀር ሃይማኖት የለውም፡፡ ነገስታት ግብዞችና ሸንጋዮችን ይወዳሉና በሽንገላው ብዛትም ወደ ንጉስ ፋሲለደስ ሄዶ ወዳጅ ሆነ፡፡ ወልደ ዩሐንስም እኔ በእንፍራንዝ አገር በሰላም እንዳለሁ ሰምቶ እንደገና እርሱ የፈረንጆች አስተማሪ ነበር፡፡ አሁንም ተሸሽጎ የፈረንጆችን ትምህርት ያስተምራል ብሎ ለእንፍራንዝ ሹም ነገረው፡፡ እኔም ስለ ሽንገላው በጣም አዘንኩ፡፡ መጀመሪያ ስለኔ የፈረንጆች ጠላት ነው ፣ በኋላም ወዳጃቸው ነው አለ፡፡ ባዘነ ልቤም እግዚያብሔር የደላይን ከንፈሮች ይቁረጣቸው  ብየ በመዝሙር  ለእግዚያብሔር ብዙ ቀን ፀለይኩ እግዚያብሔርም ሰማኝ፡፡ ይህም ሰው በብዙዎቹ  የደምቢያ አድባራት ላይ ተሾመ፡፡ ሰዎች ጠልተው ገደሉት ፡፡ እሬሳውም በቤት ወድቆ  ተገኝ፡፡ ገዳዩም አልተገኝም፡፡ ሹመቱና ገንዘቡንም ባእድ ወረሰው፡፡
በሃይማኖት ስለመጣው መቅሰፍትና የፋሲለደስ ታሪክ
በ 1635 ዓ/ም በህዝብ ሃጢያት እና ፍቅረቢስነት ፍቅር ማጣት በኢትዮጵያ ሁሉ ትልቅ እረሃብ ብርቱ መቅሰፍት ሆነ፡፡ ንጉስ ሱስንዮስና የአቦነ አልፎንዝን ሃይማኖት የተቀበሉ ሃይማኖታቸውን ያልተቀበሉ ወንድሞቻቸውን መጀመሪያ ገደሉ፣ አባረሩ፡፡ የተሰደዱትም በኋላ ከጠላቶቻቸው ብዙዎቹን ገደሉና አፀፋ መለሱ፡፡ በኋላቸውም ሆነ በፊታቸው የእግዚያብሔር ፍርሀት እንደሌለና የሰላምንም መንገድ እንዳላወቋት በግልፅ ታወቀ፡፡ በከንቱም ክርስቲያኖች ተባሉ እየሱስ ክርስቶስ ግን ከሁሉ አስቀድሞና ከሁሉ በላይ ክርስቲያኖችን እርስ በርሳቸው እንዲፋቀሩ አዟቸዋል፡፡ ይህ ፍቅር የተባለው ግን ክርስቲያኖች በተባሉት መካከል ፈፅሞ ጠፋ፡፡ ሁሉ ወንድሞቻቸውን ይበድላሉ፡፡ እርስ በርሳቸው እንደ እህል አበላል ይዋዋጣሉ፡፡ ፋሲለደስም በመልካም ምክርና ጥበብ መንገስ ጀመረ፡፡ ነገር ግን ደም በማፍሰስ አመፀኛ ንጉስ ሆኖ በክፋቱ ፀና እንጅ መልካሙን አልመረጠም፡፡ መንግስቱን በመልካም ጥበብ ያበጁለትን መልካም ቤቶችና ምሽጎች የሰሩለትን ፈረንጆች ጠላቸውና አባረራቸው፡፡ በመልካም ፋንታ ክፉ መለሰላቸው፡፡ ይህም ፋሲለደስ በሁሉም ክፉ አድራጊ ሆነ፡፡ ሰዎችንም አለፍቅር አለፍርድ ገደለ፡፡ ዝሙትንም አበዛ፡፡ ሴቶችን ዝሙቱን ከፈፀመባቸው በኋላ ገደላቸው፡፡ አመፅ የሚሰሩ ሰራዊቶችን ሁሉ እየሰደደ  የድሆችን ቤትና አገሮች አስወረረ፡፡ እግዚያብሔርም ለክፉዎች ሕዝቦች ክፉ ንጉስ ሰጣቸው፡፡ በንጉሱና በሕዝቡ ሀጢያትም ረሃብና መቅሰፍት መጣ፡፡ ከረሃብ በኋላ ቸነፈር ሆነና ብዙዎቹ ሞቱ፡፡ ሌሎችም ለመዳን ያልሆነ ፍርሃት ፈሩ፡፡ በእብደታቸው ፀንተዋልና ግማሾቹ አቡነ አልፎንዝን ስላባረራችሁት የእግዚያብሔር መቅሰፍት በላያችሁ መጣ አሉ፡፡ ግማሾቹ ደግሞ የቀድሞዋን ሃይማኖት ስለከዳችሁ ቤተክርስቲያን ስላረከሳችሁ ይህ መቅሰፍት መጣ እየተባባሉ እርስ በረሳቸው ተጣልተው ተለያዩ፡፡ እግዚያብሔር ለሁሉ ፍጥረት የሰራውን እውነተኛውን  ሥራ ፍቅረ-ቢስ የሰው ስርዓት ሰላፈረሱና ስለተላላፍ መቅሰፍት እንደመጣባቸው አላወቁም፡፡ ሃይማኖት እንዲህ ነው ወይም እንዲያ ነው የሚለውን ስለሰው ሕግጋት ሲሉ ዋና ዋና ሕግጋትን ሻሩ፡፡
ኢሳያስም ወንጌል ስለነርሱ ተናገረ፡
"እነዚህ ህዝቦች በአፋቸው ያከብሩኛል፡፡ በልባቸው ግን ከእኔ እጅግ ይርቃሉ፡፡ ሰውን ስርዓትና ትምህርት እያስተማሩም በከንቱ አመለኩኝ" አለ፡፡
ደግሞ ዩሐንስም፡
"በብርሃን አለሁ እያለ ወንድሙን የሚጠላ ዋሾ ነውና እስከዛሬ በጨለማ ይኖራል፡፡ወንድሙን የሚወድ ግን በብርሃን ይኖራል፡፡ በእርሱ ዘንድ እንቅፋት የለም፡፡ ወንድሙን የሚጠላ ደግሞ አይኖቹን ጨለማ አሳውሮታልና በጨለማ ይመላለሳል፡፡ ወዴት እንደሚሄድ አያውቅም፡፡" አለ፡፡
ይህም ትንቢት በሀገራችን ሰዎች ላይ ተፈፀመ፡፡ የሚሄዱበትን አያውቁምና ስለሃይማኖታቸው ይጣላሉ፡፡ የሚያምኑትን አያውቁምና በጨለማ ይኖራሉ፡፡ እኛ ግን በረሃብ ጊዜ ወርቃችን ካለቀ በኋላ እግዚያብሔር ምስጋና ይድረሰው ከብቶቻችንና ልብሶቻችንን ሸጠን በላንና የተራቡትን፣ የታመሙትን አበላን እንጅ እንደ ሌሎች አልተራብንም፡፡ አራት አመት ሆነው ረሃብን ቸነፈር አልተራብንም  አልታመምንም፡፡ በክፉ ቀኖች አያፍሩም በረሃብ ጊዜም ይጠግባሉ የተባለው በእኛ ላይ ተፈፀመ፡፡ ቁጥር የሌለው መልካምም ለኛ ስላደረገልን እግዚያብሔርን አመሰገንነው፡፡
ስለ ጌታየ ሀብቱ ሞትና የልጁ ታሪክ
ካንድ አመት በኋላ ጌታየ ሀብቱ ሞተብንና እጅግ አዘንን፡፡ ትልቅ ለቅሶ አለቀስን እሱ ሳይሞት ጠርቶ ይኸው እኔ እሞታለሁ እግዚያብሔር ይጠብቃችሁ ይባርካችሁና አንተም ለልጆቼ አባት ሁናቸው አለኝ፡፡ አንድ በሬና አንድ በቅሎም ሰጠኝ፡፡ ለሚስቴም ሁለት ላሞች ከነልጆቿ ሰጣት፡፡ ስለነፍሴ ፀልዩ ብሎን በእግዚያብሔር ሰላም ሞተ፡፡ እርሱ በተባረከች ነፍሱ አረፈና በትልቅ ክብርም ቀበርነው፡፡ የበኩር ልጁ ወልደ ሚካኤል የተባለውም እንደ አባቱ ወደደኝ፡፡ ምክሬንም ይሰማ ነበር፡፡ ስሟ ወለተ ጴጥሮስ ፋንታየ የተባለች ሚስትም ነበረችው፡፡ እርሷን የከበረች የክቡራን ወገኖች ነበረች፡፡ መልካም ምግባርና ሰው ወዳጅ ትህትና የሞላች ናት፡፡ እናት ልጅዋን እንደምትወድ ትወደን ነበር፡፡ ሁለቱ የጌታየ ሀብቱ ልጆች ተሰማና ምትኩ አድገው ዳዊት ማንበብ አወቁ፡፡ ምትኩ ግን እንደገና ሰዋሰው መፃህፍት አወቀና በፅኑ ፍቅርና እውቀት ከእኔ ጋር አንድነት ያለው ሆነ፡፡ እርሱ ሚስጥሬን ሁሉ ያውቃል፡፡ ለእርሱ የሸሸኩት የለም፡፡ ብዙ ጊዜ ከለመነኝ በኋላ ስለፍቅር ብየ ይህችን ትንሽ መፅሃፍ ፃፍኩ፡፡
የዘርዓ ያዕቆብ የፍፃሜ ታሪክ
ልጄም አድጎ ያማረ ጎበዝ ሆነ፡፡ ሃያ ዓመትም በሆነ ጊዜ እርሱ ባለማወቅ ወደ ምንኩስና እናዳዘነበለ አወቅሁ፡፡
"ይህ ስራ ፈጣሪ ለኛ የሰራልንን ሥርዓት ያፈርሳልና አይገባም" ብየ ብዙ ተቆጣሁት፡፡ "ነገር ግን በተፈጥሯችን ስርዓት ሚስት አግብተህ ኑር" አልኩት፡፡
"እሺ ሚስት ስጠኝ" አለኝ፡፡
ላምጌ ከተባለው አገር መድሃኒት የተባለች የአርብቶ አደሮችን አለቃ ያማረች ልጅ ፈልጌ አገኝሁ፡፡ ልጄም በእርሷ ተደሰተ፡፡ አባቷም አስራ አምስት ከብቶችና ልብሶችም ሰጣት፡፡ ለልጄም ሚስት ሆነችው አብረውም በፍቅር ነበሩ ፡፡ ከሁለት አመትም በኋላ ወንድ ልጅ ወለደች፡፡ ደስታየ አልኩት፡፡ መልሳም ሴት ልጅ ወለደች ዋጋየ አልኳት፡፡ ከመልካም ሁሉ ያጠገበኝ እግዚያብሔርን አመሰገንኩት፡፡ እኔም ለሰዎች ክርስቲያን እመስላቸው ነበር፡፡ ነገር ግን በልቤ እርሱ እንዳስታወቀኝ የሁሉ ፈጣሪና የሁሉ ጠባቂ በሆነ በእግዚያብሔር ካልሆነ በስተቀር በማንም አላምንም፡፡ አማኝ ሳልሆን አማኝ እመስላለሁ፡፡ በእግዚያብሔር ዘንድ ይህ ያስቀጣኝ ይሆን? ብየ አሰብኩ፡፡ ሰዎችን እንዲህ አታልላቸዋለሁ፡፡ ሰዎችን ማታለል ይገባልን? አልኩ፡፡ እውነቱን ብነግራቸው ለሰዎች ትልቅ ጥፋት ካልሆነ በስተቀር ሃሳቤን መግለፄ ጥቅም የለውም፡፡ ሊሰድቡኝና ሊያባርሩኝ ካልሆነ በስተቀር አይሰሙኝም፡፡ ስለዚህ እነርሱን መስየ ከሰው ጋር እኖራለሁ አልኩ፡፡ እርሱ እንዳስታወቀኝ በእግዚያብሔር ዘንድ ኖርኩ፡፡ ከኔ በኋላ የሚመጡ እንዲያውቁ ግን እስክሞት ድረስ በእኔ ዘንድ ሸሽጌ የምይዘውን ይህን መፅሃፍ በተማሪየ ገፋፊነት ልፅፍ ወደድኩ፡፡ ከሞቴ በኋላ አዋቂና መርማሪ ሰው ቢገኝ ግን በሃሳቤ ላይ ሃሳቡን እንዲጨምርበት እለምነዋለሁ፡፡ ይኸው እኔ ከዚህ በፊት ያልተመረመረውን መመርመር ጀመርኩ፡፡ የሃገራችን ሰዎች በእግዚያብሔር ረድኤት አዋቂዎች እንዲሆኑ፣ እውነትንም ወደማወቅ እነዲደርሱ፣ ሐሰትን እንዳይፈልጓትና አመፃንም ተስፋ አድርገው ዝም ብለው ከከንቱ ወደ ከንቱ እንዳይሄድ እውነትን እንዲያውቁና ወንድሞቻቸውን እንዲወዱ፣ እንግዲህ እስከ አሁን እንደሚደርጉት በከንቱ በሃይማኖታቸው እንዳይጣሉ እኔ የጀመርኩትን አንተ ጨርሰው ይህንን ያወቀና ከዚህም የተሻለ እሚያውቅ ቢገኝ ያስተምረውና ይፃፈው፡፡ እግዚያብሔር እንደ ልቡ ይስጠው፡፡ ፈቃዱን ሁሉ ይፈፅምለት፡፡ እኔ እንዳጠገበኝ ሥፍር በሌለው መልካምም ያጥግበው፡፡ እኔን እስከ ዛሬ ብፁዕ አድርጎ እንዳስደሰተኝ በዚህ ምድር ብፁዕ አድርጎ ያስደስተው፡፡ በዚህ መፅሃፌ ከኔ በላይ እሚሳደብና እንዲያምርለት የሚፈልግ ግን እግዚያብሔር እንደ ምግባሩ ይስጡ አሜን፡፡

                                                    ተፈጽመ ዛቲ መፅሃፍ

No comments: